በጉራጌ ዞኖች የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች እና የወሰን ማስከበር ስራ አፋጣኝ እልባት ይሻሉ!፡፡

    By jemil sani

    በጉራጌ ዞኖች የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች እና የወሰን ማስከበር ስራ አፋጣኝ እልባት ይሻሉ!፡፡

    የጉራጌ አካባቢ በቅርብ ጊዜ ታሪክ በዚህ ልክ በፀጥታ ስጋት እና ድንበር ዘለል ጥቃቶች የተፈተነበት ጊዜ ያለ አይመስልም። ለአመታት ሰላማዊ ቀጣና ሆኖ በኖረው አካባቢ አሁን ላይ ከ5 በላይ ቋሚ የፀጥታ ኃይል ስምሪት የሚፈልጉ የግጭት ስጋት ያንዣበባቸው አካባቢዎች ተፈጥረዋል። ኢንሴኖ፣ ሶዶ ወረዳዎች፣ ዳርጌ፣ ወልቂጤ፣ እና ቆስየ ተከታታይነት ባለው የፀጥታ ስጋት ውስጥ ይገኛሉ። ችግሩ ከስጋትነት አልፎ የአያሌ ንፁኃን ዜጎቸ ህይወት እየቀጠፈ ይገኛል።
     
    በኢንሴኖ ዙሪያ ያለው ችግር ከ5 አመታት በላይ መፍትሄ ሳያገኝ አሁንም በአሰቃቂ ሁኔታ የንፁሃን ህይወት እየተቀጠፈ ነው። የችግሩ ዋነኛ መነሻ የ11/9 ቀበሌዎች ጥያቄ ቢሆንም መንግስት ይህንን ጥያቄ በሐገራችን በሌሎች አካባቢዎች መሰል የይገባኛል ጥያቀዎች በተፈቱበት ህዝበ ውሳኔ እና ውይይት ከመፍታት ይልቅ በየጊዜው ፖለቲካዊ ፍጆታ በተጫነው እርቅ በማተኮሩ ችግሩ እየተባባሰ ሄዷል። እርቅ ተፈፅሟል በተባለበት ማግስት በርካቶች ህይወት፣ አካላቸውና ንብረታቸውን እየተነጠቁ ይገኛል።  በዚሁ አካባቢ ከመጋቢት 21 እስከ ነሐሴ 26, 2016 ዓ.ም  ህጻናትና  ጨምሮ 32 ወንዶችና 12 ሴቶች በጠቅላላው 44 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከ6000 በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል እንዲሁም ከ36 ሰዎች በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡
     
    ቆስየ ሌላው በጉራጌ አካባቢ የፀጥታ መደፍረስ የተፈጠረበት አካባቢ ነው። የዚህ አካባቢም ችግር ከአመት አመት መፍትሄ ሳይሰጠው የቆየና በአካባቢው ሙሉ ለሙሉ መንግስታዊ መዋቅር ፈርሶ በጎበዝ አለቆች እጅ የገባ ነው። ቆስየ በህግና በታሪክ የጉራጌ ዞን አካል ቢሆንም ላለፉት 5 አመታት ከዞኑ ቁጥጥር ውጪ በሌሎች አካላት ቁጥጥር ስር ይገኛል። ጉራጌዎች በርስታቸው ባዳ ተደርገው ከአካባቢው እንዲሰደዱ ተደርገዋል። በአካባቢው ሌሎች እንዲሰፍሩበት እየተደረገ ይገኛል። ሙሉ መንግስታዊ አገልግሎት ከመቋረጡ የተነሳ አካባቢው በጎበዝ አለቆች እጅ በመውደቁ የአካባቢው  ነዋሪ ለከፋ ሰብአዊ መብት ጥሰት ተጋልጧል። ነባር የገበያ ቀኖች ሳይቀር ተቋርጠዋል። ግብር የሚሰበስበውም ከዞኑ ውጭ ያለ አካል ነው።
     
    ዳርጌ አካባቢ ከዞኑ የፀጥታ ኃይል አቅም ውጪ ሆኖ የመከላከያ ሰራዊት ወደ አካባቢው እንዲገባ ተደርጓል። በአካባቢው መደበኛ የእርሻ እና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ ደረጃ ታውከዋል። እዚህ አካባቢ በተፈጠረው ችግር በርካቶች ለስደት እና ለእስር እየተዳረጉ ይገኛል።
     
     
    በሶዶ ወረዳዎች ያለው ሁኔታም ከምስራቁ ዞን የፀጥታ ኃይል አቅም በላይ ሆኖ ህዝቡ የመከላከያ ሰራዊት የእለት ተእለት ጥበቃ የሚፈልግ ሆኗል። በሁለቱ ወረዳዎች የሚገኘው ህዝብ የወትሮ ሰላምና ደህንነቱ ርቆት እራሱን አደራጅቶ ለመጠበቅ ቢሞክርም በተደጋጋሚ በሚፈፀመው የታቀደና የተደራጀ ጥቃት ሳቢያ ከፍተኛ ጉዳት እያስተናገደ ነው። እገታ እና ዘረፋው እልባት አላገኘም። እገታው የኃይማኖት አባቶችና ገዳማትን ሳይቀር ኢላማ ያደረገ ነው። እዚህ አካባቢ ያለው ችግር በከፍተኛ ትጥቅ እና ቅንጅት የታገዘ ጥቃት መሆኑ ብቻ ሳይሆን አድማሱም ሰፋ ያለ ነው። ሰዎች ከቤታቸው ታግተው ይወሰዳሉ፣ ይደበደባሉ፣ ይገደላሉ።  ብዙ ጊዜ ደግሞ ለማስለቀቂያ ተብሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ይጠየቃሉ። በዚህ መልኩ እስካሁን በሚሊዮኖቸ የሚቆጠር ገንዘብ ከህዝብ ተሰብስቦ ለአጋቾች ተሰጥቷል። በመንገደኞች ላይም ድንገተኛ ጥቃቶች በመክፈት እገታዎች ሲፈፀሙ ተስተውሏል።
     
    በሁለቱ የሶዶ ወረዳዎች ከጥቅምት 2015 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 28 2016 ዓ.ም 10 ሰዎች በታጣቂዎች ተገለዋል፣ ከ23 በላይ የሚበልጡ ሰዎች ድብደባ ተፈጽሞባቻ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ከ16 በላይ የታገቱ ገበሬዎች፣ የሃማኖት አባቶችና ነዋሪዎች ለማስለቀቂያ ከ2,900,000 ብር በላይ ከፍለዋል፡፡
     
    ወልቂጤ ከተማ ከወሰን ማስከበር ጋር የተከሰተው አለመግባባት ምንም ዓይነት ዕልባት ባለማግኘቱ አካባቢው እንደ ቀደሙት ጊዜያት ሁሉ ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋት አይሏል። በከተማዋ ላይ የሚፈፀመው የወሰን ጥሰትና ህገ ወጥ እንቅስቃሴ አሁንም መረን በለቀቀ ሁኔታ እየቀጠለ ነው። የዞኑና ከተማው አመራር ለዚህ መሰረታዊ ስርዓት አልበኝነት ዕልባት ከመስጠት ይልቅ በእለት ተለት የገፅታ ግንባታ ስራዎች ተጠምደዋል። በአካባቢው የሰፈረው የፀጥታ ኃይልም ይህንን ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ለማስቆም አልቻለም/አልፈለገም። በወልቂጤ ከተማ የፖሊስ የመሳሪያ ግምጃ ቤትን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ላይ ዝርፊያ ተፈፅሟል። ይህን ህገ ወጥ እንቅስቃሴ እየተደረገ ያለው ከጉራጌ ዞን ተነጥሎ በራሱ ልዩ ወረዳ በተደራጀው አዲሱ ልዩ ወረዳ ሲሆን በከተማው ላይ  አዳዲስ የቀረጥ ጣቢያዎች አቋቁሟል። የትራፊክና የፀጥታ ኃይል ስምሪት አድርጓል። ይህ ኃይል በከተማው ተጨማሪ የትራንስፖርት መናኸሪያ ከማቋቋሙ በላይ በከተማው አንዳንድ አካባቢዎች ከነጋዴዎችና ነዋሪዎች ግብር መሰብሰብ ጀምሯል። ክልሉ፣ ዞኑም ሆነ ከተማ አስተዳደሩ ይህንን ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ለማስቆም አንዳች ጥረት ሲያደርጉ እየታየ ባለመሆኑ ህዝቡ በከፍተኛ ቁጭትና ስጋት ውስጥ እየገባ ይገኛል።
     
    በቀቤና ልዩ ወረዳ እንዲካለሉ የተደረጉ ጉራጌዎች ከፖለቲካዊ ተሳትፎ ሙሉ ለሙሉ እንዲገለሉ ተደርገው በመሬታቸው ባይተዋር ተደርገዋል። ቀቤና በልዩ ወረዳነት እንዲደራጅ መደረጉ የምንደግፈው ጉዳይ መሆኑ ከዚህ በፊትም የገለፅነው ጉዳይ ቢሆንም የልዩ ወረዳው ምስረታ በልዩ ወረዳው ያሉትን ብዙሃን ጉራጌዎች መብት የጨፈለቀ መሆኑ ግን ተቀባይነት የሌለው ነው። ልዩ ወረዳው ውስጥ የሚገኙ ጉራጌዎች ስልታዊ በሆነ መልኩ ከመሬታቸው እየተፈናቀሉ፣ በማንናቸውም መንግስታዊና ህዝባዊ መድረኮች እንዳይሳተፉ አፈና እየፈፀመባቸው ይገኛል። በተለይም ከልዩ ወረዳው ምስረታ በኋላ ባለው ሂደት ከፖለቲካዊ መገለል ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መገፋት እየደረሰባቸው ይገኛል። ነዋሪዎች መታወቂያ፣ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ፣ ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር የመሳሰሉ አገልግሎቶች እንዳያገኙ እየተደረጉ ይገኛል።
     
    በዞኖቹ ያሉት የፀጥታ ችግሮች በአብዛኛው ድንበር ዘለል ጥቃቶች ናቸው። በጉራጌ አካባቢ የሸኔ እና የፋኖ እንቅስቃሴ መኖሩ የክልሉ መንግስት ይፋ ያደረገው ጉዳይ ቢሆንም ክልሉ በስማቸው ያልጠራቸውና መነሻቸው ከዚሁ ክልል የሆኑ ሌሎች ፅንፈኛ ኃይሎች መኖራቸው መዘንጋት የለበትም።
     
    በጉራጌ ህዝብ ላይ በ5 ግንባሮች ጥቃት እየተፈፀመ ቢሆንም ችግሩ በሌሎች ሐገራዊ ግጭቶች ተሸፍኖ ተገቢውን ትኩረት እያገኘ አይደለም። ችግሩም ከመቆም ይልቅ አድማሱን እያሰፋ የሚደርሰው ጥፋትም በዚያው ልክ እየጨመረ ይገኛል። በቂ የፀጥታ ኃይል ባለመመደቡ፣ የተመደቡትም ከወገንተኝነት በራቀ መልኩ ችግሩን ለመቆጣጠር ባለመቻላቸው በቀላሉ በቁጥጥር ስር መዋል የነበረባቸው ችግሮች እየተወሳሰቡ ይገኛሉ። ህዝቡ እነዚህ ሁሉ ችግሮች እየተጋፈጠም ቢሆን ሰላሙን ለመጠበቅ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ይገኛል። ሆኖም ህዝቡን ከጥቃት መታደግ ያልቻለው መንግስት ህግ ይከበር፣ ህዝብ ከጥቃት ይጠበቅ ብለው ፍትሃዊ የህዝብ ብሶት በሚዲያ  የሚያስተጋቡ በርካታ ሰዎችን ለወራት አስሮ እያንገላታ ይገኛል። ጉዳዩ በጣም አሳዛኘ የሚያደርገው በጉራጌ ህዝብ ላይ ግልፅ ጦርነት አውጀው ግጭት ሲመሩ የነበሩ ሰዎች አልተያዙም ወይም ተይዘው ተለቀዋል። በርካታ የጉራጌ ተወላጆች ግን አሁንም ያለ አግባብ በእስር እንዲማቅቁ እየተደረገ ነው።
     
    ሁሉም ወገኖች እንደሚረዱት ጉራጌ ከሌሎች ጋር አብሮ የመኖር ችግር የለበትም። በታሪኩ ተጠቂ እንጂ አጥቂ ሆኖ አያውቅም። ተገፊ እንጂ ገፊ ሆኖ አያውቅም። ግጭትን እና ደም መፋሰስን የሚሸሽ፣ ድንገት ከተፈጠረም በማይደገም መልኩ በሽምግልናና እርቅ የመቋጨት የተደራጀ ባህላዊ ስርዓት አለው። የእርስ በእርስ እና ከአጎራባች ወንድም ህዝቦች ጋር በመሬትም ይሁን በሌሎች ምክንያቶች የሚነሱ አለመግባባቶች ለመፍታት የሚያስችል የተመሰከረለት ችግር ፈቺ ባህላዊ ስርዓት ባለቤት ነው። ይህ ሆኖ እያለ በዋናነት በጉራጌ የፖለቲካ ልሂቅ እና በገዢው መንግስት ውድቀት ሳቢያ ህዝቡ ጠባቂ አጥቶ እየተጠቃ ይገኛል። በተለይም ከአዲሱ ክልል ምስረታ ጀምሮ የሚስተዋሉ ተከታታይና ወሰነ ሰፊ ጥቃቶች አዲሱ ክልል ከጥንስሱ ጀምሮ ጉራጌን ለማዋከብና ለመክበብ በአንዳንድ የፖለቲካ ቡድኖች የተጠመደ መረብ ነው የሚለው ጥርጣሬ የሚያጠናክሩ ናቸው።
     
    አዲሱ አደረጃጀት ጉራጌ በአንድነት ቆሞ በራሱ ጉዳይ እንዳይመክር በ2 የተለያዩ መዋቅሮች እንዲበታተን በማድረግ ለጥቃት ተጋላጭ አድርጎታል። ያለ ፍላጎቱ በሁለቱ ልዩ ወረዳዎች የተጨፈለቀው ህዝብም በሐገሩና በርስቱ ጭሰኛ የሆነበት ሁኔታ ፈጥሯል። የጉራጌ ህዝብ የተነጠቀውን ህገ መንግስታዊ መብት ለማስመለስ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ጥያቄውን እያቀረበ ይሁን እንጂ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም ይሁን በሌሎች ክልሎች ከሚኖሩ ወንድም ህዝቦች ጋር ምንም አይነት ቅራኔ የለውም። ሆኖም ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከተመሰረተ ጀምሮ አካባቢው ተከታታይነት ባለው ግጭት እየታመሰ ይገኛል። ይህ ሁኔታ የጉራጌ ህዝብ የራሱን ክልል ለማደራጀት የሚያደርገው ትግል ምን ያህል በተጨባጭ ምክንያቶች ላይ የተመሰረተ መሆኑ የሚያሳይ ነው። በመሆኑም:‐
     
    በምስራቅ መስቃን እና ማረቆ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው የ11/9 ቀበሌዎች ጉዳይ በህዝበ ውሳኔ መፍትሄ እንዲያገኝ በማድረግ ህዝቡ በመረጠው ወረዳ እንዲተዳደር ማድረግ
     
    የምስራቅ አበሽጌ ወረዳ ለማደራጀት በህዝቡ የቀረበው ጥያቄ መንግስት ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ አፋጣኝ እልባት እንዲሰጠውና ህዝቡን ከአላስፈላጊ እንግልት እንዲታደግ
     
    በቆስየ አካባቢ የተፈጠረው ወረራ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ መንግስት በወራሪዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድና የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ፣ እንዲሁም በአካባቢው የጉራጌ ዞን መንግስታዊ ተቋማት መደበኛ ስራቸውን እንዲጀምሩ እንዲደረግ
     
    በሶዶ ወረዳዎች ማለትም በሪፌንሶ፣ አማውቴ፣ ጢያ፣ በዱግዳ ቀላ እና ሌሎች አካባቢዎች ላይ የሚፈፀመው ዝርፊያ፣ እገታ እና አግቶ ገንዘብ መቀበል ለማስቆም ተጨማሪ የመከላከያ ሰራዊት ስምሪት እንዲደረግ። ይህ ማድረግ የማይቻል ከሆነ የአካባቢው ወጣቶች መደበኛ ስልጠናና ትጥቅ አግኝተው በምስራቅ ጉራጌ ዞን መንግስት የፀጥታ መዋቅር ስር ሆነው ህዝቡን ከጥቃት እንዲከላከሉ እንዲደረግ
     
    የወልቂጤ ወሰን ማስከበር ጉዳይ አፋጣኝ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል። አዲሱ ክልል ነባሩ የደቡብ ክልል ሲከተለው ከነበረው ችግርን እያንከባለሉ ከማሳደር ይልቅ ከዚህ በፊት በፌደራልና በክልል መንግስታት ተሳትፎ የፀደቁትን የከተማው መዋቅራዊ ፕላንና ወሰን ላይ የተመሰረተ የወሰን ማስከበር ስራ እንዲሰራ እናሳስባለን።
     
    የሐገር ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ የመንግስት ዋነኛ ተልዕኮ እንደመሆኑ ይህንን መሰረታዊ ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ባልቻሉ በየደረጃው በሚገኙ የመንግስት አካላት ላይ ተጠያቂነት የማስፈን ስራ እንዲሰራ
     
    ህዝቡ በዚህ ሁሉ ወከባ እና ጥቃት ውስጥ ሲገባ ህግ ይከበር፣ ህዝብ ከጥቃት ይጠበቅ በሚል መንግስት ኃላፊነቱን እንዲወጣ በመቀስቀስ የዜግነት ግዴታቸውን በመወጣታቸው ምክንያት የታሰሩ የጉራጌ የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እንጠይቃለን።

    ጎጎት ለጉራጌ!
    ጎጎት ለኢትዮጵያ!

    Search

    GOGOT

    We are dedicated to uplifting the quality of life for all ethiopians

    And together we can do just that

    Languages

    Copyright ©2023 gogot.org